Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን ውብና ምቹ ከማድረግ ባለፈ ገቢ ማስገኛ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን ውብና ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በዚህም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ተከትሎ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ በመንግሥት የተወሰደው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተጨባጭ ውጤቶች የተገኙበት ነው፡፡

በተለይም ሪፎርሙ ያመጣቸው ተጨባጭ ውጤቶች በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪነትንና አምራችነትን የሚያበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሪፎርሙ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት እንዲሁም ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን ውብና ምቹ ከማድረግ ባለፈ ነዋሪው ከልማቱ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ሀገራዊ መሰረተ-ልማቶችን 171 ሺህ 622 ኪሎ ሜትር ማድረስ ችሏል ብለዋል፡፡

የከተሞች ገቢን ከማሳደግ አኳያ ባለፉት ሦስት ወራት ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 14 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 13 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን ከ96 በመቶ በላይ አሳክቷል ነው ያሉት፡፡

ሚኒስቴሩ በተለይም በክረምት በጎ ፈቃድ የመኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት በሚለው አቅጣጫ በተቋማትና በግለሰቦች በሩብ ዓመቱ 9 ሺህ 700 የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችን መስራት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version