Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኮደርስ ስልጠና ከ31 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የምሥክር ወረቀት ወሰዱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮደርስ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙት ከ246 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል እስከ አሁን ከ31 ሺህ የሚልቁት ብቃታቸው ተረጋግጦ የምሥክር ወረቀት መውሰዳቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በዚህም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ተከትሎ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ሪፎርሙ በተሟላ መልኩ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ገበያውን ክፍት የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ መነቃቃት እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ በተለይም በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የሚሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከናወነው ሪፎርም በተሟላ መልኩ መተግበሩ የሚያድግና የተነቃቃ ፍላጎት መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ለማሳደግና ችግር ፈች ሥራዎችን ለመሥራት የተጀመረው የኮደርስ ቴክኖሎጂ ኢንሼቲቭ ትኩረት እንደሚሰጠውም አመላክተዋል፡፡

በስልጠናው ከ246 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበው እየሰለጠኑ እንደሚገኙና ከእነዚህ ውስጥ 31 ሺህ የሚሆኑት ብቃታቸው ተረጋግጦ ጠምሥክር ወረቀት መውሰዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የኮደርስ ስልጠና የሚወስዱ ወጣቶችንና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩና የመፍጠር አቅም ያላቸው ስታርትአፖች በልዩ ሁኔታ እንደሚደገፉም ነው ያነሱት፡፡

ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና ማልማት፣ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በሂደት መቀነስ በትኩረት እንዲሠራባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

 

Exit mobile version