የሀገር ውስጥ ዜና

የፌደራል ፖሊስ የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ መምሪያዎችና አባላት እውቅና ሰጠ

By ዮሐንስ ደርበው

October 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በ2016 ዓ.ም የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ መምሪያዎችና አባላት እንዲሁም አጋር ተቋማት እውቅና ሰጥቷል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት÷ተቋሙ የወንጀል መከላከል ስራን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ በውጤታማነት እየመራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የአመራሩን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ አቅም ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው÷ በትጥቅና በሎጂስቲክስ የተሻለ አቅም ለመፍጠርም ይሰራል ብለዋል፡፡

የፌደራል ወንጀል መከላከል አጠቃላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው÷ ተቋሙን በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ ብቁ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ጥረትም በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ መድረኮች፣ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሰው ሃይል አቅምን ለማሳደግም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጋር በመነጋገር የፌደራል ፖሊስ አባላት ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ለመምሪያዎች፣ በግዳጅላይ በጀግንነት ገድል ለፈጸሙ በሕይወት ላሉና በመስዋዕትነት ላለፉ አባላት እና ተቋሙን በብቃትና በታማኝነት አገልግለው በጡረታ ለተሰናበቱ የቀድሞ አባላት እውቅና ተሰጥቷል።

በዘመን በየነ