ስፓርት

ማንቼስተር ሲቲ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ተጥሎበት የነበረው እገዳ ተነሳለት

By Tibebu Kebede

July 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ማንቼስተር ሲቲ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ተጥሎበት የነበረው እገዳ ተነሳለት።

ክለቡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን የገንዘብ አስተዳደር (የፋይናንሺያል ፌር ፕሌይን) ባለማክበር እንዲሁም ከፈረንጆቹ 2012 እስከ 2016 ከስፖንሰር ሺፕ አግንቸዋለሁ በሚል ለአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ያቀረበው የገንዘብ መጠን የተሳሳተና የተጋነነ ነው በሚል ለእገዳ መዳረጉ ይታወሳል።

በተጨማሪም የክለቦችን የገንዘብ አስተዳደር የሚቆጣጠረው የማህበሩ አካል ለሚያደርገው ማጣራት ተባባሪ አይደለም በሚል ለሁለት አመታት በማንኛውም አህጉራዊ ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ከዚህ ባለፈም 30 ሚሊየን ዩሮ በገንዘብ ቅጣት መልክ እንዲከፍልም በማህበሩ እንደተወሰነበትም ይታወቃል።

የኢትሃዱ ክለብም ባለፈው የካቲት ወር ላይ የተጣለበትን እገዳ ተከትሎ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) በመውሰድ ይግባኝ በሚል አቤቱታ አቅርቦ ነበር።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ሲመለከተው ከቆየ በኋላ በዛሬው እለት ክለቡ ከቀረበበት ክስ ነጻ መሆኑን አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ሲቲ ከገንዘብ አስተዳደር ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ማህበሩ ሊያደርግ ባሰበው ማጣራት ላይ ተባባሪ እንዳልነበር አስታውሶ በሌሎች ጉዳዮች ግን ነጻ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ይህን ተከትሎም ከአውሮፓ ትላልቅ ውድድሮች እንዳይሳተፍ ተጥሎበት የነበረው እገዳ ተነስቶለታልም ነው ያለው።

በተጨማሪም የገንዘብ ቅጣቱ ከ30 ወደ 10 ሚሊየን ዩሮ ዝቅ ተደርጎለታል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በበኩሉ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም በስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚል ይጠበቃል።

ምንጭ፡- ቢቢሲ