አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች የሚመልስና ወቅቱን የዋጀ የፖለቲካ እመርታን ማረጋገጥ እንደሚገባ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አመራርና አባላት እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ “የፖለቲካ እመርታ፤ ከዴሞክራሲ መብት ወደ ሀገራዊ ሃላፊነት”በሚል ርዕስ ገለጻ አቅርበዋል፡፡
በገለጻቸውም÷በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያልተረጋገጠበት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ያላገኙበት፣ ቁልፍ ፓለቲካዊ ተቃርኖዎችና ችግሮች ያልተፈቱበት ነበር ብለዋል።
ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄድ እንደሚገባ ገልጸው÷ይህ የፖለቲካ ሪፎርምም ተቃርኖዎችን ሊያስታርቅ የሚችል የመሀል ፖለቲካን የሚከተል፣ የህዝቦችን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች የሚመልስ፣ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ብልፅግናዋን ሊያረጋግጥ የሚችል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓትን እና ተቋማትን መገንባት እንዲሁም ይህን መምራት የሚችል ለፈተናዎች የማይንበረከክ ፅኑ እና ፈተናዎችን ወደ እድል እየቀየረ የሚሰራ አመራር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውንም የም/ቤቴ መረጃ ያመላክታል፡፡፡