አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩብ ዓመቱ የኢትዮጵያን የግብርና ልማት የሚያሳኩ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተፋጠኑ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ ግብር ትግብራ በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በተለይ የግብርናውን ዘርፍ የሚደግፉ የመስኖ ልማት ስራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብሎም ምርትን ለውጭ ገበያ በስፋት ማቅረብ የሚቻለው ከተለመደው የግብርና አሰራር በመላቀቅ ዓመቱን ሙሉ በማምረት ነው ብለዋል።
ለዚህም የመስኖ ልማት ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያን የግብርና ልማት ፍላጎት እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ከዚህ ቀደም ተጀምረው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በመለየት በአጭር ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ለመስኖና የቆላማ አካባቢዎች ልማት ትኩረት በመስጠት የአሰራርና የአመራር ለውጥ በማድረግ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በሩብ ዓመቱ በተሰሩ ስራዎች በተለይ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ከነበሩባቸው ማነቆዎች ተላቀው በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠናቀቅ በሚችሉበት ቁመና ላይ እንዲገኙ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የመልማት አቅም የሚያግዙ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም ነው የገለጹት።