የሀገር ውስጥ ዜና

ከየትኛውም አቅጣጫ ሊከፈቱ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል የሚችል የአየር ሃይል ተገንብቷል- ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ

By Shambel Mihret

October 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ ሊከፈቱ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል የሚችልና የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀልበስ የሚያስችል የአየር ሃይል ተገንብቷል ሲሉ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌ/ጀ ይልማ÷አየር ሃይሉን ከነበረበት ውድቀት ለማንሳት በጸጥታ ዘርፉ የተሰሩት ሪፎርሞች ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በሰው ሃይል ግንባታ፣ በትጥቅና በውጊያ መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡

ለሀገር የሚመጥን ታላቅ የአየር ሃይል የመገንባት ጥረትን ዕውን ለማድረግና የነገውን ጠንካራ አየር ሃይል ለመገንባት ከምልመላ ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ፣ ከፖለቲካና ሌሎች ተፅዕኖዎች ነፃ የሆነ፣ ኢትዮጵያን የሚመስል ስብጥር ያለው አመራርና ባለሙያ እየተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ያሉትን የአየር ሃይል ትጥቆች ከማሻሻል ባለፈ ዓለም የደረሰባቸው ዘመናዊ ትጥቆችን እየታጠቅን እንገኛለን ያሉት ዋና አዛዡ÷በቅርቡ ከአፍሪካ ጠንካራ አየር ሃይሎች ጎን መሠለፍ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከሁሉም ሀገራዊ የጸጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንና ለጋራ ተልዕኮ በጋራ የመስራት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለሀገር መስዋዕትነት ከፍለው ሀገርን ያቆዩና ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ክብር እንደሚገባቸው ማውሳታቸውንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡