የሀገር ውስጥ ዜና

በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 619 ሺህ የሥራ እድል ተፈጥሯል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

By Mikias Ayele

October 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ለ619 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በዚህም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ተከትሎ በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡ ተመላክቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በመንግሥት የተወሰደው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በርካታ ጉዳዮችን የሚነካ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ሚና ትልቅ መሆኑን ገልጸው የሥራ እድል ፈጠራ በዋናነት በግሉ ዘርፍ የሚመራ በመሆኑ አምራች ዘርፉን የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፉት ሦስት ወራት 619 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸው፤ የተፈጠረው የሥራ እድል በሀገር ውስጥ፣ በውጭ እንዲሁም በርቀት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ያልነበረው የርቀት ሥራ በተወሰኑ ሰዎች በተንጠባጠበ መልኩ እንደነበር አስታውሰው በሩብ ዓመቱ በተደራጀ መንገድ 26 ሺህ ገደማ ዜጎች መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ዜጎችም እስካሁን 2 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ተናግረው፤ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ36 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አመላክተዋል።

ዜጎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን ራሳቸውን አብቅተው ወደ ሥራ የሚገቡበት የኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ሥርዓት ትልቅ እድል መፍጠሩንም አንስተዋል።

የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ 800 ሺህ ገደማ ዜጎች ሥልጠና መውሰዳቸውን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።

በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አንዱ የመወዳደሪያ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣሪዎችም በቀላል መንገድ የሰለጠነ ባለሙያ የሚመለምሉበት እድል መፈጠሩንም አመላክተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በአዳዲስ መስኮች ጭምር ዜጎችን ለማሰልጠን የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የ 5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ትልቅ ውጤት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ እስካሁን በመርኃ ግብሩ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ሰልጥነው ሰርቲፊኬት መቀበላቸውን ጠቁመዋል።