Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ2016/17 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት 20 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016/17 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት 20 ሚሊየን የሚጠጋ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2016/17 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

በዚህም በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ ግብር ትግብራን ተከትሎ ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካቾች ውስጥ በግብርና መስክ የተመዘገበው ስኬት አንዱ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለግብርና ልማት ትልቁ የትግበራ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በዚህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት በ2 ሚሊየን ሄክታር ብልጫ በማስመዝገብ በመኸር ወቅት 20 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰብል መሸፈን የተቻለበት ስኬታማ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2015/16 ዓ.ም የመኸር ወቅት 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኖ ነበር፤ በዚህ ዓመትም 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈን የተቻለበት ስኬታማ ጊዜ ነው ብለዋል።

በመጪው የመስኖ ስንዴ ምርታማነት ወቅትም አስፈላጊውን የግብዓት አቅርቦት ዝግጅት በማድረግ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሰብል ምርት ብክነት በመቀነስ ከ2015/16 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር በተያዘው የመኸር ወቅት በ100 ሚሊየን ኩንታል ምርት ብልጫ ያለው ሰብል ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የገባችበት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያ መርኃ ግብርም ለግብርናው ዘርፍ ወጪ ምርት ዕድገት ከፍተኛ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በተያዘው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ የ796 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት የዕቅዱን 103 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በተለይም 115 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሩብ ዓመቱ 519 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማስገኘት በመጠንም ሆነ በገቢ አቅም ስኬታማ እንደሆነ አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም በሕገ-ወጥ መንገድ ይወጣ የነበረን የቡና ምርት ሕጋዊ መስመር በማስያዝ በሩብ ዓመቱ ከቡና ወጪ ንግድ የተገኘው ስኬት በመጠንም ሆነ በውጭ ምንዛሬ ገቢ አቅም ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም የቁም እንስሳት ሕገ-ወጥ ንግድ ሥርዓትን መስመር በማስያዝ በእንስሳት ወጪ ንግድና በሥጋ ወጪ ንግድ ከተያዘው ዕቅድ በላይ ስኬት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት 20 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ መሰራጨቱን አስታውሰው፤ ለ2017/18 ምርት ዘመን የመኸር ወቅትም ከወዲሁ 24 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በዚህም ካለፈው ዓመት ትምህርት በመውሰድ በአሁኑ ሰዓት የስድስት መርከብ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version