የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረሪ ክልል ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ 

By Mikias Ayele

October 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ፕሮጄክቶቹ ሶስት የመስኖ ግድቦች፣ የአርሶ አደሮች የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከል፣ ድልድይ፣ ሼዶች፣ የጤና ቢሮ ማስፋፊያ እና የመድሀኒት ማከማቻ ህንፃ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በምረቃው ላይ እንደገለፁት÷ ሰብዓዊ እና ኢከኖሚያዊ ልዕልናን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ሀያል ሀገር ለማደረግ እየተሰራ ይገኛል።

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና እራስን በመቻል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

እስካሁን ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ የተቀመጠው ግብ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ ገልጸው÷ ስንዴ አምርቶ ወደ ውጭ መላክ መቻሉ ለተመዘገበው ውጤት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት ልማቶች በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት በማጎልበት የተሻለ ስኬትን የሚያጎናፅፉ ናቸው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡