አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የ2016 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡
“በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የተገኘበት መሆኑ ተገልጿል።
በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ6 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታና እድሳት፣ ችግኝ ተከላ፣ የወጣቶች ትምህርትና ስልጠና፣ ደም ልገሳና የከተማ ጽዳት ተግባራት መከናወናቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ርዚቅ ኢሳ÷ በበጎ ፈቃድ አገልገሎቱ ከ16 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ግልጋሎት መስጠት መቻሉን ጠቅሰው፤ የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት፣ ዞኖችና ከተሞች እውቅና ተሰጥቷል።
በደሳለኝ ቢራራ