የሀገር ውስጥ ዜና

ጥቃት ለመፈፀም በተንቀሳቀሱ 60 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት ላይ እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ እስር ተቀጡ

By Mikias Ayele

October 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሌ ክልል አፍዴር እና ሸበሌ ዞኖች በኩል ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 60 የአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ እስራት መቀጣታቸው ተገለጸ።

ፖሊስ በ60 የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ በቂ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃ በማቅረብ በሽብር ወንጀል ምርመራ አጣርቶ ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ተዘዋዋሪ ችሎት በ10 መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቷል።

በዚህም ሁለት የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በዕድሜ ልክ እስራት፣ 56 ተከሳሾች እንደወንጀል ተሳትፏቸው ከ6 ዓመት እስከ 18 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል።

እንዲሁም በአልሸባብ የሽብር ቡድን አባልነት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ እያንዳንዳቸው 2 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲፈረድባቸው ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል፡፡

በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአልሸባብ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ቤዝ ለመመስረት፣ ከአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ወጣቶችን በመመልመል፣ በሶማሊያ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ ሰላማዊ ሰው መስለው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ በማድረግ፣ ለሽብር ቡድኑ በመሰለል፣ ፈንጂ በማፈንዳት ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም አካባቢዎችን የሚቆጣጠር ኃይል ለማዘጋጀት ሲንቀሳቀስ እንደነበር የምርመራ ቡድኑ ባካሄደው ማጣራት ደርሶበታል ብሏል የፖሊስ መረጃ፡፡

የሽብር ቡድኑ ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከሶማሊያ በሰባት ተሸከርካሪና በአራት ሞተር ሳይክል በሌሊት ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሁሉል አካባቢ ሲደርስ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ከአራት ቀን እልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ በርካታ የሽብር ቡድኑን አባላት መደምሰሱ ይታወሳል።

በዚህም ሁለት ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ 92 የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችን በመማረክ 406 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ67 ሳጥን መሰል ጥይቶች፣ 43 ላውንቸር እና 27 ብሬን ከአንድ ሳጥን መሰል ጥይት ጋር እንዲሁም በርካታ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በኤግዚቢትነት መያዛቸውን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በስድስት የምርመራ መዝገብ 95 ተጠርጣሪዎች በሽብር ወንጀል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡