አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ17ኛ መደበኛ ስብሰባው ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ ባደረገው ውይይት፤ በሩብ ዓመቱ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን ገምግሟል።
በጎፋ ዞን ያጋጠመው የተፈጥሮ አደጋ ተጎጂዎችን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ወደ ቋሚ መጠለያ ማሻገር መቻሉ በስኬት የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ የተከበሩ የብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓላት፣ ወንድማማችነትንና ሕብረ-ብሔራዊነትን ባጎለበተ መልኩ፣ ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው መከበራቸው የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎች ውጤታማነት የሚያሳይና የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል።
ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት በመኽር እርሻ የሰብል ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ልዩ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት በመታየት ላይ መሆኑ ተነግሯል።
የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ለጉዳት እንዳይዳረግ ያለብክነት በዘመቻ የመሰብስ ስራን ጨምሮ ለቀሪ የመኽር እርሻ ስራዎች ተገቢው ትኩረት በመስጠት ርብርብ እንዲደረግ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ለግብርና ልማት ስራዎች፣ በንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራት፣ የዋጋ ንረት ቁጥጥርና ክትትል፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፣ የኮዲንግ ስልጠና፣ የኮሪደር ልማት፣ የትምህርት ስራዎች፣ የበሽታ መከላከል ስራዎች፣ የገቢ አሰባሰብ ስራን ማጠናከር በቀጣይ ልዩ ትከረት እንዲሰጣቸው ምክር ቤቱ አሳስቧል።
በክልሉ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግል ባለሀብቱን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በማሰማራት ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ መሆኑ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።
በኢንዱስትሪ፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፍ ለማልማት መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ አልሚዎች መስተዳድር ምክር ቤቱ ፈቃድ መስጠቱም ተገልጿል።