አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሂዝቦላህ ቡድን በእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ መኖሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረ የድሮን ጥቃት መሰንዘሩ ተገለፀ፡፡
የእስራዔል ጦር እንዳስታወቀው÷ ዛሬ ጠዋት ላይ ከሊባኖስ የተላኩ ድሮኖች በቄሳሪያ ከተማ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በከተማዋ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰምቷል፡፡
በጥቃቱ በከተማዋ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ መኖሪያ ዒላማ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፤ በአካባቢው በሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተመላክቷል፡፡
የእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጥቃቱ በተሰነዘረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባላቤታቸው በአካባቢው እንዳልነበሩ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ሁለት ድሮኖች ከሊባኖስ ተነስተው በከተማዋ ጥቃት ለመፈፀም እየበረሩ በነበረበት ወቅት በእስራዔል አየር ሀይል ተመትተው ወድቀዋል ተብሏል፡፡
ጥቃቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁን ለመግደል በማለም በኢራን የተቀነባበረ ነው ሲል የሀገሪቱን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ኢየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።