Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች 2ኛው ዙር ስልጠና ተጠናቀቀ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “የህልም ጉልበት ለዕመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው 2ኛው ዙር ስልጠና በስኬት መጠናቀቁ ተገለፀ።

የስልጠናው ዋና ዓላማ አመራሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የውጭ ግንኙነት ሥራዎችንና የተቋማት ግንባታ ውጥኖችን ከሀገራዊ ህልም እና ከብሔራዊነት ትርክት ጋር አስተሳስሮ የአገልጋይነት ስነ-ምግባራዊ አመራርን መሰረት ባደረገ መልኩ በውጤታማነት ተግባራዊ እንዲያደርግ ለማስቻል ነው ተብሏል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ በአጠቃላይ 22 ሺህ 715 የሚሆኑ የፓርቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በ11 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች ለ10 ቀናት የተሰጠውን ስልጠና መውሰዳቸውን አስፍረዋል፡፡

ስልጠናው የአመራሩን እውቀት፣ ክህሎት እና ልምድ ከማዳበሩም በተጨማሪ ፓርቲውንና እና መንግስትን የሚያጠናክሩ፣ ችግር ፈቺ እና ለቀጣይ የብልፅግና ጉዞ አጋዥ የሆኑ ገንቢ ሀሳቦችን በግብዓትነት የተገኘበት መሆኑንም አቶ አደም ገልጸዋል።

በቀጣይም አመራሩ በስልጠናው ላይ በተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በራስ ጥረት የበለጠ አቅሙን አዳብሮ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰላም፣ በዲፕሎማሲ፣ በተቋምና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ይበልጥ ለማቀጣጠል አስተዋፆ ለማበርከት እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

አቶ አደም “ስልጠናውን የተከታተላችሁ አመራሮች የቀሰማችሁትን እውቀት፣ ክህሎት እና ልምድ ከሚትመሩት ተቋምና አከባቢ ጋር በማስተሳሰር ፍሬያማ በሆነ መልኩ መሬት ላይ በማውረድ እቅዶቻችንን በተሳካ መልኩ ለመፈፀምና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተምሳሌታዊ አብነታችሁን እንድትወጡ አደራ ለማለት እወዳለሁ” ሲሉም ገልፀዋል።

የስልጠናው ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስተዋፆ ላበረከቱ ተቋማትና አመራሮች በተለይም በአስተባባሪነት፣ በአሰልጣኝነት እና በአወያይነት ለተሳተፉ እንዲሁም በጠንካራ ዲሲፕሊን ስልጠናውን ለተከታተሉ የፓርቲው አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

Exit mobile version