የሀገር ውስጥ ዜና

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሩብ ዓመቱ የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሩብ ዓመቱ የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉ ተገለጸ።

የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መካሄድ ጀምሯል።

በተያዘው በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የማስመዝገብ ውጥን መያዙን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በ2017 የመጀመሪያው 100 ቀናት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉን ጠቅሰው÷ ይህም የተቀመጠው እድገት እንደሚመዘገብ አመላከች ነው ብለዋል።

በተለይ በወጪ ንግድ፣ በመንግስት ገቢ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አብራርተዋል።

ከወጪ ንግድ አንጻር በተለይ በወርቅ ወጪ ንግድ እጅግ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን 4 ቶን ብቻ እንደነበር አስታውሰው÷ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ 7 ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ለውጥ ማምጣቱን አመላካች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀደም ተብሎ ሰፊ ዝግጅት ተደርጎበት በመተግበሩ ስኬታማ መሆኑን ገልጸው÷በተለይ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የተከናወኑ ስራዎች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በትይዩ ገበያና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን አሁን ላይ እጅግ የተቀራረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ያለፉት ሶስት ወራት አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመዘገብ ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ የገቢ መሰብሰብ አቅም እያደገ መምጣቱን የተናገሩት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው÷ በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እጅግ አበረታች የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በሩብ ዓመቱ 180 ቢሊየን ብር ገቢ ከታክስ መሰብሰቡን ጠቅሰው÷ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ71 ቢሊየን ብር እድገት እንዳለው አብራርተዋል፡፡