አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከብሪክስ አባል ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ጋር በሞስኮ በነበራቸው ቆይታ÷ የሩሲያ እና ኢዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ግንኙት በተመለከተ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ጠንካራ ሐይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍም የሀገራቸው ኩባንያዎች በኢነርጂ ዘርፍ በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልጉ ገልጸው÷ በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ የሚመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በሩሲያ መማራቸውን ጠቁመው÷ በቆይታቸውም የሩሲያን ቋንቋ፣ ባህል እና ወግ አውቀው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በሩሲያ-አፍሪካ ግንኙነት እና በደቡብ ለደቡብ ትብብር በጥበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡