የሀገር ውስጥ ዜና

ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በሚነሡ የተዛቡ መረጃዎች ላይ ግልፅነት ተፈጥሯል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By amele Demisew

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “በአዲስ አበባ እየተተገበረ ካለው የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በሚነሡ የተዛቡ መረጃዎች ላይ ከነዋሪዎቹ ጋር ግልፅነት ፈጥረናል” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ ከከተማዋ ነዋሪዎችና ከልማት ተነሺ ተወካዮች፣ ከታዋቂ እንዲሁም ከሐይማኖት አባቶች ጋር በኮሪደር ልማት ሥራ ሂደት ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ÷ ከኮሪደር ልማት አስፈላጊነት ጋር ተያይዞ ያሉ ጥንካሬዎች፣እጥረቶች ፣የተለያዩ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች መነሳታቸውን ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

“ከልማት እና የህዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ዉጪ ምንም ድብቅ አጀንዳ ስለሌለን ሁሉንም መረጃ እና አሰራር በዝርዝር አቅርበን ግንዛቤያቸውን የሚጨምሩ እና የመረጃ ክፍተቶችን የሚሞሉ እንዲሁም ላነሱዋቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆኑ ማብራሪያዎች ሰጥተናል” ሲሉም ገልጸዋል።

ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በሚነሡ የተዛቡ መረጃዎች ላይም ግልፅነት ፈጥረናል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ።

ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ቆርጠን እየሰራን እና ያረጁ ቤቶችን እየቀየርን የዜግነት ክብርን ማረጋገጥ ላይ ስለመሆናችን የግንዛቤ ችግር ባይኖርም የልማት ፍላጎቱ ግን ዕለት በዕለት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

የለዉጥ መንገድ አልጋ በአልጋ ስለማይሆን ጊዜያዊ ችግሮችን ተቋቁመን መሰረታዊ ለወጥ ለማምጣት በጋራ መትጋት እንዳለብን ተግባብተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በልማቱ ትብብር እያደረጉ ላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባዋ “ለከተማችን ብልፅግና ያለ እረፍት በፍጥነት መስራታችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡