Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያን ማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያን ማጎልበት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር)፣ የናይሮቢ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍራንክ ሚዋቲና የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ናቸው።

ስምምነቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑና ለካፒታል ገበያው ተሳታፊዎች በጋራ ስልጠና መስጠትን ጨምሮ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን እንደሚያካትት ተገልጿል።

የሚኖረው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለውን የካፒታል ገበያ ማጎልበት የሚያስችልና የእውቀት ሽግግር፣ አቅም ግንባታና ድንበር ዘለል ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጥላሁን ካሳሁን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ስምምነቱ ከኬንያ ተሞክሮ ለመውሰድና በዘርፉ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ነው።

የካፒታል ገበያን ስርዓት ለመገንባት የገበያውን ስነ-ምህዳር መረዳትን እንደሚጠይቅ አንስተው÷ ስምምነቱ አስፈላጊውን ስነ-ምህዳር ለማወቅ ያስችላል ብለዋል፡፡

ፍራንክ ሚዋቲ በበኩላቸው ስምምነቱ የሀገራቱን የውስጥ ገበያ ከማጎልበት ባለፈ ቀጣናዊ ንግዶችን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

 

Exit mobile version