የሀገር ውስጥ ዜና

በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለፀ

By amele Demisew

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ ዓመት በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ የሀገር ሃብት መዳኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን÷በዚህ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተቋማቸው ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ የሀገር ሃብት ማዳኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ሰርጎ በመግባት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የአሸባሪና የፅንፈኛ ቡድን አባላት ከእነ ኢግዚቢታቸው በቁጥጥር ስር ውለው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም በጥናት ላይ የተመሰረተ ኦፕሬሽን ተካሂዶ በርካታ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተጣርቶባቸው በፍርድ ቤት እንዲቀጡ መደረጉን መግለጻቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተቋሙ የተጀመሩ አዳዲስና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እየተመሩ እንደሆነና ከተያዘላቸው ጊዜ በፊት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አመላክተዋል፡፡