የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ ሹመቶችን ሰጡ

By ዮሐንስ ደርበው

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ለሦስት ከፍተኛ ኃላፊነቶች ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሰላማዊት ካሳ የቱሪዝም ሚኒስትር እንዲሁም ሃና አርዓያሥላሴ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመዋል፡፡

በቅርቡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው በተሰየሙት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ቦታ የተተኩት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የፍትሕ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰላማዊት ካሳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ እንዲሁም ሃና አርዓያሥላሴ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡