Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የያህያ ሲንዋር መገደል የጦርነቱ ፍጻሜ አይደለም-  ጠ/ሚ ኔታንያሁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል የሃማስ መሪ የነበሩትን ያህያ ሲንዋርን ጋዛ ውስጥ መግደሏን አረጋግጣለች፡፡

ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ÷ የያህያ ሲንዋር መገደል ከፍተኛ ድል ቢሆንም የጦርነቱ ፍጻሜ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በሀማስ እገታ ሥር የሚገኙ እስራኤላውያን እስከሚለቀቁ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በርካታ እስራኤላውያን እንዲገደሉ እና እንዲታገቱ በተደረገበት የጥቅምት 7 ጥቃት የያህያ ሲንዋር ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንስተው÷ የመሪው መገደል በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ሊቀይረው እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የያህያ ሲንዋር መገደል ለእስራኤል ብሎም ለአሜሪካ ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸው÷ የመሪው መገደል ምን አልባትም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል፡፡

በአንጻሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢራን ልዩ መልዕክተኛ በበኩላቸው÷ የያህያ ሲንዋር መገደል እስራኤልን ከምን ጊዜውም በላይ ለመፋለም የሚያነሳሳ የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠናል ብለዋል፡፡

ሁኔታው ጦርነቱን ከማብረድ ይልቅ ሊያባብሰው እንደሚችልም ነው ያስረዱት፡፡

Exit mobile version