የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ልማት ባንኮችን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተካሄደ

By ዮሐንስ ደርበው

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የጀርመን ልማት ባንክ በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱን ያደረጉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት እመቤት መለሠ (ዶ/ር) እና የባንኩ ማኔጅመንት አባላት ከጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ከጀርመን ኤምባሲ እንዲሁም ከጀርመን ልማት ባንክ የተወጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት ናቸው፡፡

የውይይቱ  ትኩረትም በጀርመን ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በሚሠሩ ሥራዎች ዙሪያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተግባራዊ የሚደረጉ እና በጀርመን ልማት ባንክ ፋይናንስ የተደረጉ ሁለት በሥራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈፃፀምም በውይይቱ  ላይ ቀርበዋል ተብሏል፡፡

እነዚህም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ማሽነሪዎች የሊዝ አገልግሎት እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርኘራይዞችን ለመደገፍ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና በባንኮች አማካኝነት የሚቀርብ የፋይናስ አቅርቦት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ካሉት በተጨማሪም በቀጣይ ወደ ትግበራ የሚገቡ ሁለት ፕሮጀክቶች የአተገባበር ሂደትን አስመልክቶ ውይይት በማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን የባንኩ መረጃ አመላክቷል፡፡