የሀገር ውስጥ ዜና

አብርሆት የትውልዶችን ልቦና በእውቀት ለማብራት የተቋቋመ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አብርሆት የትውልዶችን ልቦና በእውቀት ለማብራት የተቋቋመ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷አብርሆት የትውልዶችን ልቦና በእውቀት ለማብራት የተቋቋመ ነው ብለዋል፡፡

በሕንፃው ምሰሶዎች ጥበብ የሚለው ቃል በ18 የራሳቸው ፊደል ባላቸው ቋንቋዎች ተፅፎ የሚገኘውም ለዚህ ተልዕኮ ያለውን ቁርጠኝነት ለማመላከት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አብርሆት ቤተመፃህፍት በብልሃት ክህሎት የተጎናፀፉ ወጣቶችን የማብቃት አላማውን በትጋት በመወጣት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

ዛሬ በአብርሆት ያገኘኋቸው ወጣቶች እንደ ሮቦቲክስ እና የፈጠራ ትግበራ ሥራዎች ላይ ተጠምደው ስላገኘኋቸው አድናቆት እና ማበረታቻ ይገባቸዋል ብለዋል።

መጪው ትውልድ ከኢትዮጰያ የልማት ግቦች ጋር በተናበበ ሁኔታ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኮዲንግ፣ በሳይበር ሴኩሪቲ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ክህሎታቸውን ማጠናከር መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል፡፡