ቴክ

ጃፓን የወጣቶችን የዲጅታል ክህሎት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓን በኢትዮጵያ የወጣቶችን የዲጅታል ክህሎት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር፣ በስታርትአፕ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታ፣ የጃፓን ኢንቨስተሮችን በማምጣት እንዲሁም በዲጂታል ልማት ላይ ያተኮረ ምክክር አድርገዋል።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከጃፓን መንግሥት ጋር ቀደም ብለው ለተጀመሩ በርካታ የትብብር ስራዎች አመስግነው፤ የጃፓን ቴክኖሎጂ ባለቤቶችና ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የልማት ስራዎችን ለመደገፍ የጃፓን መንግስትና ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የወጣቶችን የዲጅታል ክህሎት አቅም ለመገንባት እንደሚሰራ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

በዚህ ረገድ ከጃይካ ጋር፣ የስታርትአፕ ልማት ድጋፍ ስራዎች እንዲሁም ከሳፋሪኮም እና ሲሚቶሞ ጋር የተጀመሩ የትብብር ስራዎችን ጠቅሰው፤ ሌሎች የትብብር ማዕቀፎችንም ለማካተት ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።