Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በማዕከላዊ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሔደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ክልሎቹ የጋራ የጸጥታና የፍትህ ግብረ ኃይል በአጎራባች አካባቢዎች ለህዝቦች ደህንነትና ሰላም እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በተለዩ ጉዳዮችና ቀጣይ እርምጃ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ነው የመከሩት።

በመድረኩ ከጅማ-ወልቂጤ-ወሊሶ እስከ ዓለም ገና አዲስ አበባ፣ ከቡታጅራ-ሌመን-ዓለም ገና-አዲስ አበባ መስመር፣ ከቡታጅራ-ባቱ-ሞጆ-አዲስ አበባ መስመሮች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚያስተጓጉሉ ጥቂት አካላት ላይ የፌደራልና የክልል መንግስታት በቅንጅት እርምጃ መውሰዳቸውም ተገልጿል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል፣ የክልል እና የአካባቢው ሚሊሻ አካላት በጋራ ባደረጉት ርብርብ ለውጥ በመገኘቱ መንገደኞች ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ምቹ አካባቢ ተፈጥሯልም ተብሏል፡፡

በተለይ ከቡታጅራ-ባቱ-ሞጆ-አዲስ አበባ መንገድ ከስጋት ነጻ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ እንደተቻለም መገለጹን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ከቡታጅራ-ሌመን-ዓለም ገና-አዲስ አበባ መንገድ የጸጥታ ኃይሉ ባከናወነው ተግባር ለውጥ የታየበት መሆኑም በመድረኩ ተጠቁሟል።

Exit mobile version