የሀገር ውስጥ ዜና

የገቢ አሰባሰቡን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር ይገባል – ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢ አሰባሰቡን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር ይገባል ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

በገቢዎች ሚኒስቴር የሐዋሳ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት አዲስ ያስገነባውን ህንፃ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የገቢ አሰባሰቡን ቀልጣፋ ለማድረግ ምቹ የስራ ከባቢን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ይህም ለግብር ከፋዮች፣ ለአመራሩና ለሰራተኛው ወሳኝ በመሆኑ በተለያዩ ቅርንጫፎች ምቹ የስራ ከባቢ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት አመት የተያዘውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩን ገልጸው፤ ዕቅዱን ለማሳካት ጠንክረን በመስራት ሀላፊነታችንን እንወጣ ብለዋል።

የሀዋሳ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ በበኩላቸው፤ ምቹ የስራ ከባቢ የዘመነ የታክስ አሰባሰብን፣ ቀልጣፋና የተሻለ አገልግሎትን ለማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዳዊት ጎሣዬ