ጤና

የጡት ካንሰር መንስዔዎችና ምልክቶች

By Feven Bishaw

October 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በጡት ውስጥ ያሉ ሕዋሳት አድገው እና ተከፋፍለው ዕጢ ሲፈጥሩ የሚከሰት ሕመም ነው።

የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር ዓይነቶች አንዱ ሲሆን÷ በአብዛኛው ከ 50 ዓመት በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ ይከሰታል፡፡

ሲጋራ እና አልኮል መጠቀም፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የሆርሞን ወሊድ መከላከያ ወይም ሌላ የሆርሞን መድሃኒት ለረጅም ጊዜ መጠቀም እና የጨረር ሕክምና ለጡት ካንሰር መከሰት ምክንያቶች ናቸው::

በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር መኖር፣ አለመውለድ ወይም የመጀመሪያ ልጅን ከ30 ዓመት በኋላ መውለድ፣ ከወለዱ በኋላ ጡት አለማጥባት፣ ከ12 ዓመት ዕድሜ በፊት የወር አበባ መምጣት እና ከ55 ዓመት ዕድሜ በኋላ የወር አበባ ዘግይቶ መቆም እንደ መንስዔ ሊወሰዱ ይችላሉ::

የጡት ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

በብዛት የሚስተዋሉ የጡት ካንሰር ምልክቶች በጡት መጠን ወይም ቅርጽ ላይ ለውጥ ማየት፣ የአተር መጠን ያለው እብጠት፣ በጡት ወይም በጡት ጫፍ ላይ የመልክ ወይም የቆዳ ለውጥ፣ ከቆዳው በታች እብነ በረድ የመሰለ ጠንካራ ቦታ መኖር ናቸው፡፡

በተጨማሪም ከጡት ጫፍ ውስጥ በደም የተበከለ ወይም ንጹህ ፈሳሽ መኖር፣ የተሰራጨ ዕጢ ከሆነ ደግሞ የደረትና የአጥንት ሕመም እና የመሳሰሉት ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የጡት ካንሰር ምርመራ ለማድረግ በዋነኛነት ማሞግራፊ፣ አልትራሳውንድ እና ፒኢቲ የተሰኙት ምርመራዎች የሚታዘዙ ሲሆን አጠራጣሪ ውጤቶች ሲገኙ ናሙና ተወስዶ ምርመራ ይደረግበታል::

ሕክምናን በተመለከተም ቀዶ ህክምና፣ ኪሞቴራፒ፣ የጨረር ሕክምና፣ የሆርሞን ቴራፒን ጨምሮ በርካታ የጡት ካንሰር ሕክምና አማራጮች እንዳሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጡት ካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ቀደም ብለው ከመጡ እና ህክምናው ከተሰጠ የመዳን ዕድሉ ከፍ ያለ በመሆኑ ማንኛውም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ያለበት ሰው በፍጥነት የሕክምና ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ።