ጤና

የፊስቱላ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአራት ክልሎች ብቻ እየተሰጠ የሚገኘውን የፊስቱላ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ ለፊስቱላ ህክምና ድጋፍ ከሚያደርገው የሂሊንግ ሃንድስ ኦፍ ጆይ ድርጅት መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አሊሰን ሺጎ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ድርጅቱ የፊስቱላ ተጋጭ እናቶች ልየታ፣ የፊቱላ ህክምና እና ያገገሙትን መልሶ በማቋቋም ወደ ማህበረሰብ እንዲቀላቀሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ እስካሁን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ሲዳማ ክልሎች የፊስቱላ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነ አስታውሰው፤ በሌሎች ክልሎችም ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በተለይም የትራንስፖርት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ሂሊንግ ሃንድስ ኦፍ ጆይ በዘርፉ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለድርጅቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የድርጅቱ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አሊሰን ሺጎ÷ ድርጅቱ እናቶች በፊስቱላ ለጉዳት ከመጋለጣቸው በፊት የመከላከል ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።