የሀገር ውስጥ ዜና

ባንኩ 13 ነጥብ 4 ኩንታል ወርቅ መግዛቱን ገለጸ

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሽረ እንዳስላሴ ቅርንጫፍ በሶስት ወራት ውስጥ ከህጋዊ ወርቅ አዘዋዋሪዎች 13 ነጥብ 4 ኩንታል ወርቅ መግዛቱን አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ባንኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ተኪኤ ግደይ እንደገለፁት÷ ባንኩ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ግዢ የፈፀመው በሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረም ወራት ውስጥ ነው።

ብሔራዊ ባንክ ቀደም ሲል በነበረው የወርቅ ዋጋ ላይ የ15 በመቶ ማሻሻያ ጭማሪ በማድረጉ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለመግዛት እንደተቻለ ገልፀዋል።

ባለፈው 2016 ዓ.ም ከመስከረም እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ባንኩ የፈፀመው የወርቅ ግዢ 303 ሺህ 213 ነጥብ 20 ግራም እንደነበር አስታውሰው÷ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ 1 ሚሊየን 349 ሺህ 32 ግራም የወርቅ ምርት ግዢ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ ባንኩ በአጠቃላይ ላከናወነው የወርቅ ግዢ በጥቅሉ ከ17 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሽረ እንዳስላሴ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተወክሎ የወርቅ ግዢ ማዕከል በማቋቋም በክልል ደረጃ የወርቅ ግዢ በመፈፀም ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡