አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ብሪታኒያ በየመን ሰነዓ በሚገኙ የሁቲ አማፂያን ዒላማዎች ላይ የተቀናጀ የአየር ጥቃት መፈፀማቸውን አስታወቁ፡፡
የሁቲ አማፂያንን የመረጃ ምንጭ ጠቅሶ አናዶሉ እንደዘገበው÷ አሜሪካ እና ብሪታኒያ በሰሜናዊ እና ደቡብ ሰነዓ በሚገኙ የሁቲ መሳሪያዎች ላይ ስድስት የአየር ጥቃቶችን ፈፅመዋል፡፡
በተመሳሳይ በምስራቃዊ ሰነዓ በሚገኙት ካህላን እና አል አብላ አካባቢዎች ዘጠኝ የአየር ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን÷ የአሜሪካ አየር ሀይል ከመሬት በታች የተቀበሩ እና በአምስት የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የአማፂያኑ የጦር መሳሪያ ክምችቶች ላይ የተሳካ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠዋል።
በጥቃቱ አማፂያኑ መርከቦችን እና ንፁሃንን ለማጥቃት የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያ ማውድም ተችሏል በማለት ገልጸው÷ ጥቃቱ የጠላት መሳሪያ ከአሜሪካ እይታ ውጭ እንደማይሆን ያሳየንበት ነው ብለዋል፡፡
በጥቃቱ በንፁሃን ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል።
የሁቲ የፖለቲካ ዘርፍ ባለስልጣን መሀመድ አል ቡኻይቲ በበኩሉ÷ ጥቃቱ ጋዛን ለመደገፍ የምናደርገውን ወታደራዊ ቁርጠኝነት የበለጠ ይጨምረዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡