የሀገር ውስጥ ዜና

ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ወርቅ በህገወጥ መንገድ ይዞ ተገኝቷል የተባለ ግለሰብ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጠ

By Shambel Mihret

October 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጥፍጥፍ ወርቅ በህገወጥ መንገድ ይዞ ተገኝቷል የተባለ ግለሰብ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አማረ ዮሐንስ በተባለ ተከሳሽ ላይ በ2016 ዓ.ም መጨረሻ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 21 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ እንዲሁም የማዕድን አዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 7 ንዑስ ቁጥር 2 ስር እና አንቀጽ 78 ንዑስ 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ በሚል ሁለት ክስ መስርቶ ነበር።

በዚህ ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ በየካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:40 ላይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ የበረራ ቦርድ አካባቢ በተደረገበት ፍተሻ በለበሰው ጃኬት ውስጥ የዋጋ ግምቱ 3 ሚሊየን 189 ሺህ 506 ብር ከ32 ሳንቲም የሆነ 1 ሺህ 10 ነጥብ 9 ግራም የሚመዝን ጥፍጥፍ ወርቅ ይዞ ተገኝቷል።

ግለሰቡ በወቅቱ በአካባቢው የነበረን የፖሊስ የሻምበል አዛዥን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ህግ ቦታ ሲወስደው ግለሰቡ ፍቃድ እንደሌለውና ነጋዴ እንዳልሆነ ጠቅሶ እንደራደር በማለት ከያዘው ወርቅ ላይ “ግማሹን ልስጥህና ልቀቀኝ” በማለት የያዘውን ወርቅ ለጉቦ ያቀረበ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ ተገቢ ያልሆነ ጉቦ ወይም ጥቅም መስጠት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

በሌላኛው ሁለተኛው ክስ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የተፈጥሮ ማዕድን መያዝ የሚል የወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ ክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰውና በንባብ ዝርዝሩን እንዲሰማ ከተደረገ በኋላ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ፤ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮችን አቅርቦ የምስክርነት ቃላቸውን አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል መርምሮ ተከሳሹን ከቀረበበት ሁለት ክሶች መካከል በሁለተኛው ክስ ብቻ ማለትም የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የፈጥሮ ማዕድን መያዝ ወንጀል እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሹ ተከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ያስተላለፈበት ፍርድ ቤቱ፤ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለማክሰኞ ጥቅምት 12 ቀን ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ