አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለዩክሬን ማጠናከሪያ የሚውል የ425 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዲሚር ዘነልስኪ ጋር በስልክ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ድጋፉን ይፋ ማድረጋቸው ተነግሯል።
በውይይታቸው ፕሬዚዳንት ባይደን ሀገራቸው የዩክሬንን ጦር ለማጠናከር ተጨማሪ አየር መከላከያ፣ ተተኳሽ እና ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ በድጋፍ ጥቅሉ ውስጥ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ሚሳኤሎች እና በአንድ ጊዜ ስድስት ያህል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ የሚችል መሳሪያ (ሂማርስ) ተካተዋል።
ድጋፉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አስተዳደር ሩሲያን ድል ለማድረግ ያወጣውን አዲስ እቅድ ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ባይደን የዩክሬንን ጦር ለማጠናከር በመጪው ህዳር ወር ከከዩክሬን ከፍተኛ የጦር አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጥሮ ይዘዋል መባሉን ኤንኤችኬ እና ሲጂቲኤን ዘግበዋል፡፡