የሀገር ውስጥ ዜና

የካፒታል ገበያው ጅማሬ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ድንቅ ክዋኔ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Feven Bishaw

October 17, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የካፒታል ገበያው ጅማሬ ኢትዮጵያን ወደ ተሳለጠና ዘመናዊ የአክስዮን ገበያ ስርዓት የሚያስገባትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ድንቅ ክዋኔ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ ሚና የሚኖረው የካፒታል ገበያ በኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ የአክስዮን ሽያጭ ስራው ተጀምሯል፡፡

ይህን ተከትሎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትሰስር ገፃቸው÷ የካፒታል ገበያ በሀገራችን ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ከማሳደጉ ባሻገር አካታች የፋይናንስ ዘርፍን በማሳደጉ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የ130 አመታት ዕድሜ ባለፀጋው ኢትዮ ቴሌኮም፤ 10 በመቶ የአክስዮን ድርሻውን በሽያጭ ለሕዝብ ማቅረቡ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያው ጅማሬ ኢትዮጵያን ወደ ተሳለጠ እና ዘመናዊ የአክስዮን ገበያ ስርዓት የሚያስገባትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ድንቅ ክዋኔ መሆኑንም ጠቅሰዋል።