Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቴክኖሎጂ ፈጠራ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድር ኢትዮጵያውያን 3ኛ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች 3ኛ ደረጃ በመያዝ 4 ሺህ ዶላር ተሸለሙ፡፡

ከ48 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ እና ታዳጊዎች የተሳተፉበት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በውድድሩም የቱኒዚያ ተወዳዳሪዎች 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ 16 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲሸለሙ÷ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 3ኛ ደረጃን በመያዝ የ4 ሺህ ዶላር ተሸላሚ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

“አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለበጎ ተጽዕኖ” በሚል መሪ ሐሳብ ከግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በነበረው ውድድር ላይ 4 ሺህ 928 ታዳጊዎች ተሳትፈዋል፡፡

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት እና አፍሪካ ሲልከን ቫሊ ባዘጋጁት በዚህ ውድድር÷ በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና በመሳሰሉ ዘርፎች ለችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ የፈጠራ ውጤቶች መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

በማጠቃለያ ውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ታንዛኒያ፣ አልጀሪያ እና ቱኒዚያ ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻው ውድድር ምርጥ ሰባት ውስጥ ተካትተው ነበር፡፡

Exit mobile version