አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮ ቴሌኮምን 10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ ይፋ አደረጉ፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም ካለው አጠቃላይ የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ 10 በመቶውን ነው በዛሬው ዕለት ለሽያጭ ይፋ ያደረገው፡፡
የእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋም 300 ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት አንድ ሰው ከ33 አክሲዮን ጀምሮ እስከ 3 ሺህ 333 አክሲዮን ድረስ መግዛት የሚችል ሲሆን÷ ይህም በብር ሲገለጽ ከ9 ሺህ 900 ብር እስከ 999 ሺህ 900 ብር ይደርሳል ማለት ነው፡፡
የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውም ከዛሬ ጥቅምት 6 ጀምሮ እስከ ታኅሣስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል፡፡
በአክሲዮን ሽያጩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ለሽያጩ ከማመልከታቸው በፊት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅደመ-ሁኔታዎች እንዳሉም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት ኢትየጵያዊ ዜጋ መሆን፣ መመዝገቢያ መተግበሪያው ላይ መመዝገብና አካውንት መክፈት፣ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሕጋዊ ሠነድ ማቅረብ መቻል፣ የግዢውን ማመልከቻ የሚያቀርቡት ለሌላ ሰው ከሆነ መወከላቸውን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ የውክልና ማረጋገጫ ሠነድ መያዝ፣ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዲሁም ከማመልከታቸው በፊት በደንበኛ ሳቢ መግለጫ ሠነድ ላይ የተዘረዘሩትን ስለኩባንያው የቀረቡ መግለጫዎች እና ስጋት ትንተናዎች በሚገባ ማንበብ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
ከዚያም በቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ ለአክሲዮን ግዥ የቀረበውን ማመልከቻ በጥንቃቄ መሙላት እና ክፍያውን በ48 ሰዓት ውስጥ ከፍለው ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅባቸው ኩባንያው አሳስቧል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው