አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 14ኛው የአፍሪካ ጠበቆች ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ማንዴላ አዳራሽ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል ።
በጉባዔው የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በጉባዔው ኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ወዲህ እያከናወነች የሚገኘው የፍትሕ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ጠበቆች ማህበራት ህብረት ም/ፕሬዚዳንት ቴወድሮስ ጌታቸው÷ ኢትዮጵያ ለህብረቱ መመስረት አስተዋጽኦ ማበርከቷን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና አንድነት ትልቅ ትግል ያደረገች ፤ለነጻነት ምሳሌ የሆነች ሀገር መሆኗንም አውስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጠበቆች ማህበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች የፍትሕ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን መብቶች እንዳይነጠቁ ጥብቅና እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ጠበቆች ማህበራት ህብረት ፕሬዚዳንት ካሪ አብዱልበጎይ በበኩላቸው÷ የአህጉሪቱ ህብረት ተገናኝቶ በዘርፉ እንዲመክር የአፍሪካ ህብረት ትልቅ ሚና መጫወቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ 14ኛውን ጉባዔ በማስተናገዷ አመስግነው÷ በመድረኩ የእውቀት ሽግግር፣ የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ አስረድተዋል፡፡
በታሪኩ ወ/ሰንበት እና ማርታ ጌታቸው