የሀገር ውስጥ ዜና

ለማረፍ ሲዘጋጅ ጭስ የታየበት አውሮፕላን በተሳካ ሁኔታ አርፏል- የኢትዮጵያ አየር መንገድ

By ዮሐንስ ደርበው

October 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በዝግጅት ላይ ሳለ ጭስ የታየበት አውሮፕላን በሰላም ማረፉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

ዛሬ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በመጓዝ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET248 አውሮፕላን ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በዝግጅት ላይ ሳለ በአውሮፕላኑ ውስጥ ጭስ መታየቱ ተገልጿል፡፡

አውሮፕላኑ በድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም በማረፍ መንገደኞችን በተለመደው መልኩ ከአውሮፕላኑ ማውረድ መቻሉን የአየር መንገዱ መረጃ አመላክቷል፡፡

አየር መንገዱ ጭሱ የተነሳበትን ምክንያት በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ÷ ለተፈጠረው ክስተት መንገደኞቹን ይቅርታ ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቁጥር ET154 ሚያዝያ 29 ቀን 2016 ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ሳለ በአውሮፕላን ውስጥ ጭስ መታየቱ ይታወሳል፡፡

በወቅቱም አውሮፕላኑ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተመደበለት የመንገደኞች ማስተናገጃ በር ያለ ምንም እክል በማረፍ መንገደኞቹ ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ ማውረዱ ይታወቃል፡፡