የሀገር ውስጥ ዜና

የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በጅማ ከተማና አካባቢው ለሚገኙ ዐይነ ስውራን አጋዥ መነጽር ድጋፍ አደረገ

By Melaku Gedif

October 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በጅማ ከተማና አካባቢው ለሚገኙ ዐይነ ስውራን ማንበብ፣ ሰው እና የተለያዩ ቁሶችን መለየት የሚያስችል አጋዥ መነጽር ድጋፍ አደረገ።

ጽ/ቤቱ ከኦርካም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሁለተኛው ዙር ለ72 የጅማ ከተማ እና አካባቢው ዐይነ ስውራን ተማሪዎች የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ አጋዥ መነጽር ድጋፍ ማድረጉን የኦርካም ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አሰግድ ክብረት ገልጸዋል።

ከጅማ እና ከተለያዩ አጎራባች ክልሎች የተውጣጡ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ቴክኖሎጂው አጋዥ ስለመሆኑ እና በቂ ስልጠናም እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በሁለተኛው ዙር ድጋፍ በሀዋሳ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ እና ጅማ ከተሞች ለሚገኙ 2 ሺህ ዐይነ ስውራን እንደተደረገም ታውቋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በመጀመሪያው ዙር ለ2 ሺህ ዐይነ ስውራን አጋዥ መነጽር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በወርቃፈራሁ ያለው