የሀገር ውስጥ ዜና

በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች በስር ፍርድ ቤት የተጣለባቸው የቅጣት ውሳኔ ተሻረ

By ዮሐንስ ደርበው

October 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች በተከሰሱበት ከሲሚንቶ ግዢ ጋር የተያያዘ የሙስና ወንጀል በስር ፍርድ ቤት የተጣለባቸው የቅጣት ውሳኔ ተሻረ።

ተከሳሾቹ ላይ በስር ፍርድ ቤት ተወስኖ በነበረው የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ አቤቱታ መነሻ መሰረት ተመርምሮ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ ተሻሽሎ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስም 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ በመንግስት ላይ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት የአገልግሎቱ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በአጠቃላይ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊየን 99 ሺህ 360 ብር ጥቅም ያገኙ መሆኑን ጠቀሶ ነበር ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበው።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት ምስክሮችን እና በተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና ሙስጠፋ ሙሳን በተከሰሱበት ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ከተሳሾቹ ጋር ቀደም ብሎ ክስ ቀርቦባቸው የነበረና ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በችሎቱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የነበረው በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ተከላክለዋል በማለት በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ አስተያየቶችን መርምሮ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ 1ኛ ተከሳሽን በ2 አመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የወሰነ ሲሆን÷ ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ 1 አመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸው ነበር።

ከሁለት ፋብሪካዎች ያለአግባብ በተፈጸመ የ29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ግዢ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ ክስ ያቀረበ ቢሆንም ችሎቱ ግን ጥቅም አግኝተውበታል በሚል ለቅጣት ዓላማ የወሰደው እያንዳንዳቸው የ700 ሺህ ብር ጥቅም አግኝተዋል የሚለውን የገንዘብ መጠንን ብቻ ነበር።

በዚህ መልኩ በስር ፍርድ ቤት በተሰጠው የቅጣት ውሳኔን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ በተጣለው ቅጣት ተገቢ ያልሆነና አነስተኛ ቅጣት መሆኑን ጠቅሶ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሎ ነበር።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የዐቃቤ ሕግ የይግባኝ አቤቱታውን ያስቀርባል በማለት በይግባኝ ባይና በመልስ ሰጪ መካከል የቀረበውን የመልስ መልስ እና የግራ ቀኝ ክርክርን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ ቀደም ሲል የስር ፍርድ ቤት የጣለውን ቅጣት ውሳኔ ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንጻር ተሽሮ ተሻሽሎ ቅጣት መጣል እንዳለበት በማመን በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው የቅጣት ውሳኔን ሽሮ አሻሽሎ በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።

ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቅጣቱን በማሻሻል 1ኛ ተከሳሸ ተስፋዬ ደሜን 5 ዓመት ከ 6 ወር እና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን፣ 2ኛ ተከሳሸ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 3ኛ ተከሳሸ ሙስጠፋ ሙሳን ደግሞ በ4 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እና በ2ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ