አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐይማኖታዊ አስተምኅሮ፣ በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሥራ እና አንድነትን በማስተማር ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን አድባራት ያገለገሉት አባ መፍቀሬ ሰብዕ ኪዳነወልድ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡
በ1921 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ተጉለት ወርቅጉር አካባቢ የተወለዱት አባ መፍቀሬ ሰብዕ በግሸን ደብረ ከርቤ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይታው በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡
በልጅነታቸው ለዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት ተከታትለው ዲቁናን ተቀብለው በትውልድ ቦታቸው አካባቢያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እስከ 14 ዓመታቸው ድረስ ማገልገላቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ከ1946 ዓ.ም ጀምሮም በወቅቱ አጠራር በወሎ ሀገረ ስብከት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል።
ከ68 ዓመታት በፊት ግሸን ላይ የማስተማር ፈቃድ ተሰጥቷቸው በጎንደርና በወሎ በበርካታ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ አስተምረዋል፡፡
ምዕመናን በማስተባበር አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነፅን ጨምሮ ከተጣለባቸው ሐይማኖታዊ ኃላፊነት ባሻገር÷ ለአረንጓዴ ዐሻራ የነበራቸው ትጋት ይጠቃሳል፡፡
በዚህም በተለያዩ አድባራት እና አካባቢያቸው ችግኝ ስለመትከል እና መንከባከብ በማስተማርና በመተግበር ኖረዋል፡፡
በሌላ በኩል ለቅርሶች መደረግ ስላለበት ጥበቃና እንክብካቤ ሲያስተምሩና ሲሟገቱ የኖሩ ስመ ጥሩ አባት መሆናቸውም ይጠቀሳል፡፡
ለአብነትም ከ45 ዓመታት በፊት በወቅቱ የነበሩትን ባለሥልጣናት በማግባባትና በማሳመን የግሸን ደብረ ከርቤ መንገድ እንዲሠራ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መንገዶች እንዲጠረጉ በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይነሳል፡፡
ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው አባ መፍቀሬ÷ በተለያዩ ሐይማኖት ተከታዮች እና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጭምር ተወዳጅ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
አባ መፍቀሬን በተመለከተ ከዚህ በፊት በፋና የተሰራውን ዘጋቢ ፊልም ለመመልከት ሊንኩን ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=UuUJgO0eEUQ