የሀገር ውስጥ ዜና

የጡት ካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው መሄዳቸው ሕመሙን አክሞ ለማዳን ተግዳሮት መሆኑ ተገለፀ

By Shambel Mihret

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው መሄዳቸው ሕመሙን አክሞ ለማዳን ተግዳሮት መሆኑ ተገለፀ፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን ÷ የጡት ካንሰር በሽታ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃም ስርጭቱ እየጨመረ እንደመጣ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያም በየአመቱ 16 ሺህ 904 ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚያዙና በየአመቱ 9 ሺህ 626 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የጡት ካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው እንደሚሄዱና ይህም ሕመሙን አክሞ ለማዳን ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ስራ አስፈጻሚዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ታካሚዎች በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ እንቅፋት ከሚሆኑት ሁኔታዎች ውስጥ ህረተሰቡ ስለበሽታዉ ዝቅተኛ ግንዛቤ መኖር እና ምርመራና ህክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው መሆኑን አንስተዋል።

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድርግ የህክምና ውጤቱን ከማሻሻሉም በላይ የታካሚዎች በህይወት የመኖር ዕድላቸውንም ከፍ በማድረጉ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ጡትን በእጅ በመዳሰስ እና በመመርመር የጡት ካንሰርን ቀድሞ መለየትና መከላከል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ የጥቅምት ወር የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ሲሆን÷ለጡት ካንሰር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችን በመገንዘብ በሽታውን መከላከል ይገባልም ተብሏል፡፡