የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

By Feven Bishaw

October 15, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ሚኒ-ባሶች፣ ሚዲ-ባስ ታክሲዎችና የከተማ አውቶብሶች ላይ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

የታሪፍ ማሻሻያው ከነገ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ቢሮው አስታውቋል፡፡

የታሪፍ ማሻሻያው ወቅታዊ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ እና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ያማከለ መሆኑን ያስታወቀው ቢሮው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አዲስ በተሻሻለው ህጋዊ የታሪፍ ተመን ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡

ይህንን በሚተላለፉ አካላት ላይ ቢሮውና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱም አስገንዝቧል።

ህብረተሰቡም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሲያጋጥሙ ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች፣ ለትራፊክ ፖሊስ እና በአቅራቢያ ባለ የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በአካል ወይም በነፃ የስልክ መስመር 9417 ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ አስታውቋል።