Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በህገ-ወጥ መንገድ ማዳበሪያ ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ስር የዋሉ የ70 ዓመት አዛውንት በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም በህገ-ወጥ መንገድ የአፈር ማዳበሪያ ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት የ70 ዓመት አዛውንት በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ አቶ ተቀባ ማሞ የተባሉ የ70 ዓመት አዛውንት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክስ ዝርዝሩ ላይ እንደተገለጸው፤ ተከሳሹ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:30 ላይ 710 ሺህ 686 ብር የሚገመት 200 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተሽከርካሪ ጭነው መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ከአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በማድረግ ሀሰተኛ ደረሰኝና የይለፍ ሰነዶችን በመያዝ ወደ ደብረ ብርሃን እየተጓዙ እንዳሉ በሸገር ከተማ ኩራ ጅዳ ክ/ከ አካባቢ ሲደርሱ በፀጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተከሳሹ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸውና በንባብ እንዲያደምጡ ከተደረገ በኋላ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎቹን አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ግለሰቡ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን፤ ተከሳሹ ግን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመር እና ተከሳሹ የ70 ዓመት አዛውንት እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ከግምት አስገብቶ በማቅለያነት በመያዝ በ3 ዓመት ከ11 ወራት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተያዘው 200 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version