የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ለ2 ሚሊየን 982 ሺህ ሕጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ተሰጠ

By ዮሐንስ ደርበው

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2 ሚሊየን 982 ሺህ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት መስጠት መቻሉን የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ከ4 ሚሊየን በላይ ሕጻናትን ለመድረስ ታቅዶ ከመስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና ጤና ሁኔታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ ጽጌረዳ አምሳሉ ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁን ድረስም ለ2 ሚሊየን 982 ሺህ ሕጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት መስጠት መቻሉን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ፖሊዮ በተበከለ ምግብና ውኃ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ፣ ለዘላቂ የአካል ጉዳትና ሞት የሚዳርግ ህመም መሆኑን አስረድተው÷ ይህን በመገንዘብ ልጆቻቸውን ያላስከተቡ ወላጆች እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክትባት ዘመቻው ዓላማ ፖሊዮን አስቀድሞ ለመከላከል መሆኑን ገልጸው÷ ለሥራው መሳካት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡