የሀገር ውስጥ ዜና

የመሬት ይዞታ መረጃ አያያዝን ማዘመን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ይቀርፋል- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

By ዮሐንስ ደርበው

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና የመረጃ ሥርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ በዘርፉ ያሉ ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮችን በማስቀረት የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ ያስችላል ሲሉ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የመሬት ልማት አሥተዳደር ቢሮን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም ቢሮው በመሬት አሥተዳደር ዙሪያ በሠራው ሪፎርም የተለያዩ ለውጦች መኖራቸው እንዲሁም የመሬት ሕጎችን ሙሉ በሙሉ የማሻሻል፣ የመሰብሰብ ሥራና ሪፎርሙን መሸከም የሚችል አደረጃጀት መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ፣ የሲስተም ልማት ሥራ፣ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እና የአሥተዳደር ሥርዓቱን የማሻሻል ተግባር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቅንጅታዊ አሠራሮች እና ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር መቻሉን ተነስቷል፡፡

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ሥራውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘርፉን ለማዘመን የተጀመረው ሥራ እንዲሳካ የአመራሩና የባለሙያው ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ በበኩላቸው የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ሥርዓቱን ማዘመን በዘርፉ የሚታየውን ኢ-ፍትሐዊ አሠራር በማስቀረት የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ድልድይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በቤዛዊት ከበደ