አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማዕከል የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ እና የመሬት ማግኔታዊ መስክ መለኪያ መሳሪያ ተከላ ተጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ ተገለፀ።
ወደ ትግበራ የገባው የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያው በተለምዶ ጂፒኤስ ተብሎ ከሚታወቀው እና ከሌሎችም መሰል አገልግሎት ከሚሰጡ ሙሉ የዓለም ሽፋን ካላቸው የሳተላይት መገኛ ስርዓቶች መረጃ መቀበል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ የማግኔታዊ መስክ መለኪያ መሳሪያው የመሬት ማግኔታዊ መስክ በጊዜ ውስጥ የሚኖረውን ለውጥ ካለማቋረጥ መለካት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመሳሪያው በእንጦጦ ተራራ ላይ መተከል በሂደት የአለም አቀፉ የማግኔቶሜትር ትስስር መረብ አንድ አካል የመሆን እድል የበለጠ እንደሚያሰፋም ነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ የሚያመላክተው፡፡
ከዚህ መሳሪያ እና ከመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያው የሚገኘው መረጃ ከሌሎች አገልግሎቶች በተጨማሪ ኢንስትቲዩቱ እያደራጀው ላለው የሰፔስ ዌዘር መከታተያ ማዕከል ወሳኝ ግብዓት ሆነው እንደሚያገለግሉም ታውቋል፡፡