የሀገር ውስጥ ዜና

ተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ በሊባኖስ እንደሚቆዩ አስታወቀ

By amele Demisew

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሊባኖስ ያሰማራው የሰላም አስከባሪ ሃይሉ በሊባኖስ እንደሚቆይ አስታወቀ፡፡

ምንም እንኳን እስራዔል የተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከሊባኖስ እንዲወጣ እየወተወተች ቢሆንም ተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይሉን ከሊባኖስ እንደማያስወጣ ይፋ አድርጓል፡፡

የተመድ ሰላም አስከባሪ ስምሪት ሀላፊ ጂያን ፒር ላክሮክስ በሊባኖስ ንጹሃን ዜጎችን ለመርዳት ሲባል ሰላም አስከባሪው ከሀገሪቱ የማይወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ተመድ ሂዝቦላህ ምሽጎችን ሲገነባ እና ሚሳኤሎችን ወደ ድንበር ሲያስጠጋ ማስቆም አልቻለም ሲሉ ከሰዋል፡፡

ተመድ በበኩሉ እስራዔል ሆን ብላ የሰላም አስከባሪውን ኢላማ በማደረግ በፈጸመችው ጥቃት አምስት ወታደሮቼ ቆስለዋል ሲል ወቅሷል፡፡

በሌላ በኩል እስራኤል በሰሜን ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት በትንሹ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ስምንት ደግሞ መቁሰላቸውን ሊባኖስ አስታውቃልች፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው አይቱ በሚባለው መንደር መሆኑ የተነገረ ሲሆን እስራዔል በበኩሏ ጥቃቱ ሂዝቦላህን ኢላማ ያደረገ ስለመሆኑ ገልጻለች።

ባለፉት ቀናት በደቡባዊ ሊባኖስ እና ጋዛ ሂዝቦላህን ዒላማ ያደረጉ ከ230 በላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የገለጸው የእስራዔል መከላከያ ሚኒስቴር፤ በርካታ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላት መገደላቸውን ጠቁሟል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡