Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም መልማቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በክልሉ የግብርና አሁናዊ ልማት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ውስጥ ከ8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታሩ በኩታ ገጠም መልማቱን ተናግረዋል።

4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ደግሞ በሜካናይዜሽን ታግዞ የለማ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በክልሉ የሜካናይዜሽን አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሰብሎች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸው፤ ከ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በበቆሎ ሰብል እንዲሁም 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በገብስ ሰብል እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን እየተሰራ ባለው ስራ በመኸር እርሻ ከ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኖ ያለ መሆኑን አንስተዋል።

ዘንድሮ በበጋ መስኖ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ የስንዴ ሰብል እየለማ መሆኑን አቶ ጌቱ አመላክተዋል።

በተጨማሪም የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ ለማምረት በተሰጠው ትኩረት በምርት ዘመኑ 528 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማ መሆኑን አንስተዋል።

ሩዝ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር በላይ ፣ ለውዝ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ፣ ሱፍ 180 ሺህ ሄክታር፣ ቦሎቄ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር፣ ሰሊጥ 500 ሺህ ሄክታር እንዲሁም ማሾ 300 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆንኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም 8 ነጥብ 7 ሚሊየን የኬሚካል አፈር ማዳበሪያ ለአርሶአደሩ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉ የስርጭት ችግሮች ለመፍታትም በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር መደረጉን አመላክተዋል።

በተጨማሪም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ላሞችና ጊደሮችን ማዳቀል መቻሉንና 53 ሚሊየን የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአርሶና ከፊል አርብቶአደሩ ማከፋፈል መቻሉን እንዲሁም 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶና ከፊል አርብቶአደሩ ማከፋፈል መቻሉን አመላክተዋል።

2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኞችን በአርሶአደሩ ማሳ መተከሉን፤ በአንድ ዓመት ብቻ ደግሞ 58 ሚሊየን የሻይ ችግኝ በ4 ሺህ 2 ሄክታር መሬት ላይ መትከል መቻሉንም አንስተዋል።

 

በመራኦል ከድር

Exit mobile version