Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ በላይ እንዳይሆን ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ በሚገዙበት እና በሚሸጡበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳሰበ።

ብሔራዊ ባንኩ ይህንን በተመለከተ ለንግድ ባንኮች በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጿል።

አዲሱ የምንዛሬ ተመን አሰራር ይፋ መሆኑን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ ያሉ ሂደቶችን ሲከታተል መቆየቱን የገለጸው ብሔራዊ ባንኩ፤ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

በመሆኑም የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበት አስታውቋል።

አሁንም ቢሆንም ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በራሳቸውና ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ስምምነት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል።

ንግድ ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በተናጠል በየቀኑ ማሳወቃቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሶ፤ ባንኮች ከውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚጠይቋቸውን ኮሚሽኖች ከምንዛሬ መሸጫ ጋር ሳይሆን በተናጠል ለደንበኞቻቸው እንዲያሳውቁሞ አዝዟል።

እስካሁን በነበረው አሰራርም ንግድ ባንኮች የምንዛሬ መሸጫ ዋጋቸውን ከኮሚሽኑ ጋር ደምረው ያስታውቁ እንደነበር አስታውሶ፤ ንግድ ባንኮች ሁለቱን ጉዳዮች እስከነገ ባለው ባለው ጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል ብሏል።

ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣ ዋጋቸውን ከመሸጫቸው ማቀራረብ እንዳለባቸው ከዚህ ቀደም በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡበት እንደነበረ ብሔራዊ ባንክ አስታውሷል።

በተለይ ባንኮች የውጭ የሚሸጡበት ዋጋ እንጂ የሚገዙበት ከጥቁር ገበያ ጋር ስለማይቀራረብ የውጭ ምንዛሬ ፍሰቱ ወደ ጥቁር ገበያ ያደላል የሚል ስጋቶችንም የሚገልጹ ነበሩ ተብሏል።

ይህም የሆነው ባንኮች የውጭ ምንዛሬን የሚገዙበትና የሚሸጡበት ዋጋ መሀል ኮሚሽን እና የመሰል አገልግሎቶችን ከግምት ስለሚያስገቡ የዋጋው ልዩነት ከፍ ያለ ሆኖ ቆይቷል ሲል ገልጿል።

Exit mobile version